የፋጢማው እመቤታችን ቤተመቅደስ

የፋጢማው እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተመቅደስ የሚገኘው በፖርቱጋል ሀገር ነው፡፡ የፋጢማው እመቤታችን ቤተመቅደስ የመቁጠሪያ እመቤታችን ባዚሊካ በመባልም ይታወቃል፡፡ ከመቁጠሪያ እመቤታችን ባዚሊካ በተጨማሪ እመቤታችን ለሦስቱ ልጆች ስትታይ በተቀመጠችበት በትልቁ የሾላ ዛፍ ስፍራ የተሠራው ሎስ ፐሬን የሚባለው ቤተጸሎት፣ የኢየሱስ ቅዱስ ልብ ሐዋልት፣ እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ለሦስቱም ልጆች ማለትም ለሉቺያ ዶስ ሳንቶስ እና ለአጎቱዋ ልጆች ጃቺንታና ፍራንቸስኮ ማርቶ ለመጀመሪያ ጊዜ በታየችበት ስፍራ የተሠራዉ ቤተጸሎት ይገኛሉ፡፡ በየወሩ 13ኛው ቀን እ.አ.አ. ከግንቦት 13 ቀን 1917 ዓ. ም. እስከ ጥቅምት 13 ቀን 1917 ዓ. ም. ድረስ ሉቺያና ሁለቱም የአጎቱዋ ልጆች እመቤታችንን ያዩአት እንደ ነበር ይነገራል፡፡ በዚያን ጊዜ ሉቺያ የ10 ዓመት ልጅ፣ ፍራንቸስኮ የ9 ዓመት ልጅ፣ ጃቺንታ ደግሞ የ7 ዓመት ልጅ ነበረች፡፡ ልጆቹ ሰለ እመቤታችን አጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም መታየት ሲተርኩ ከርሷ መምጣት በፊት "የሰላም መልአክ" ይታያቸው እንደ ነበረም ይናገሩ ነበር፡፡ ይኸው "የሰላም መልአክ" ድሮም ማለትም ከእመቤታችን ማርያም መታየት በፊት እ.አ.አ. በ1916 ዓ. ም. ታይቷአቸው እንደ ነበረም ይተርካሉ፡፡ ሉቺያ በበኩሏ ስለ እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም መታየት ስትናገር፣ "ማርያም ከፀሐይ የበለጠ ብሩህ ብርሃን ያላት፣ ከመስተዋት ድንጋይ በበለጠ ሁኔታ ብርሃን የምታስተላልፍ፣ በሚያንጸባርቅ ውኃ የተሞላች፣ በሚያቃጥሉ የፀሐይ ጮራዎች የተከበበች ነበረች" ብላለች፡፡

 

ከሉቺያ ምስክርነት እንደምንረዳው እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ለሦስቱም ልጆች በመጀመሪያ ያለቻቸው "ኃጢአተኞችን ለማዳን ተጋድሎ አድርጉ" ነበር፡፡ በዚህ ዐይነት ወገባቸውን በጣም አጭር በሆኑ ገመዶች ይታጠቁ ነበር፡፡ በጣም ሙቀታማ በነበሩ ቀናትም ውኃ መጠጣት ይተው ነበር፡፡ ብዙ ተመሳሳይ የተጋድሎ ተግባራት ይፈጽሙ እንደ ነበረ ይነገራል፡፡ ከሁሉም እጅግ በጣም ጠቃሚ መልእክት፣ እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም በፋጢማ የመታየቷ ምስክር ለነበሩ ለሦስቱም ልጆች አበክራ አደራ ያለቻቸው የመቁጠሪያ ጸሎት በየቀኑ እንዲደግሙ ነበር፡፡ ይኸውም ለዓለም ሰላም ሆነ ለግል ሰላምም ቢሆን የመቁጠሪያ ጸሎት ወሳኝ ነገር መሆኑን እንዲረዱ ለልጆቹ ደጋግማ እንደ ተናገረችም ከቤተመቅደሱ ታሪክ ለመረዳት እንችላለን፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም የታየቻቸው ልጆች ዘመዶች ሳይቀሩ በዚያን ጊዜ የአንደኛው ዓለም ጦርነት ተዋጊዎች ነበሩ፡፡ ሉቺያ ዶስ ሳንቶስ ከዓመታት በኋላ እንደ ተረከችው በሁለተኛው የመታየቷ ዕለት ማለትም እ.አ.አ. በሰኔ 13 ቀን 1917 ዓ. ም. እመቤታችን እጅግ ቅድሰት ድንግል ማርያም ጃቺንታና ፍራንቸስኮ በልጅነታቸው እንደሚሞቱ ተናግራ ነበር፡፡

 

ሉቺያም በበኩሏ ቶሎ ብለሽ ጃቺንታንና ፍራንቸስኮን ወደ ሰማይ ውሰጂአቸው እንዳለቻትና እመቤታችንም፣ "በርግጥ በቶሎ ወደ ሰማይ እወስዳቸዋለሁ፤ አንቺ ግን በዓለም ላይ ትንሽ ትቆዪአለሽ፡፡ ምከንያቱም ጌታ ኢየሱስ እኔ በዓለም ላይ እንድታወቅና እንድወደድ ይፈልጋልና፡፡ በአንቺም አማካይነት በዓለም ላይ የእኔ እጅግ ንጹሕ ልብ አክብሮት እንዲስፋፋም ይፈልጋልና" እንዳለቻትም ከሉቺያ ምስክርነት ለመዳት ይቻላል፡፡ በርግጥም ፍራንቸስኮና ጃቺንታ ከእምቤታችን በፋጢማ ከመታየት ሁለት ዓመት በኋላ ማለትም እ.አ.አ. በ1919 ዓ. ም. እንደ ሞቱ ከፋጢማው የእመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተመቅደስ ታሪክ ለመረዳት ይቻላል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ  እ.አ.አ. በግንቦት 13 ቀን 2000 ዓ. ም. ፍራንቸስኮስና ጃቺንታ ብፁዓን ናቸው ብለው በይፋ አውጀዋል፡፡

 

ስለ ሦስቱ የፋጢማ ምስጢሮች ከተነሣ ደግሞ፣ በአንደኛው ምስጢር እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ለሦስቱም ልጆች የገሃነመ እሳትን አሰቃቂ ሁኔታ እንዳሳየቻቸው መስክረዋል፡፡ በሁለተኛው ምስጢር ደግሞ ስለ አንደኛው ዓለም ጦርነት መጠናቀቅና ስለ ሁለተኛው ዓለም ጦርነት መጀመር እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ለሦስቱም ልጆች ነግራቸዋለች፡፡ በተጨማሪም፣ በሁለተኛው ምስጢር ራሺያ ለእመቤታችን ማርያም እጅግ ንጹሕ ልብ የተለየ እንዲሆን እንደምትፈልግም ነግራቸዋለች፡፡ ብዙዎቹ እንደሚገምቱት ይህንን የእምቤታችን የእጅግ ቅድስት ድንግል ማርያምን ምኞት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እ.አ.አ. በመጋቢት 25 ቀን 1984 ዓ. ም. ተግባራዊ አድረገዋል፡፡ ይኸውም የተባበሩት የሶቪየት መንግሥታት እ.አ.አ. በታህሳስ 26 ቀን 1991 ዓ. ም.  ከመበታተናቸው በፊት ለመላው ዓለም ለራሽያም ጭምር ሐዋርያዊ ቡራኬአቸውን በመስጠት ነበር፡፡ የፋጢማ የሦስተኛው ምስጢር በቫቲካን ተደብቆ የቆየ ሲሆን አንድ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ከሌሎች ብዙ ጳጳሳትና ካህናት ጋር በመስቀል ሥር በተራራ ላይ በወታደሮች እንደሚገደሉ ይናገር ነበር፡፡ ቤተክርስቲያን ሦስተኛውን ምስጢር እ.አ.አ. በግንቦት 13 ቀን 1981 ዓ. ም. ቱርካዊው ታጣቂ፣ መሐመት ዓሊ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስን ለመግደል በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ካደረገው ሙከራ ጋር ታያይዘዋለች፡፡ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ራሳቸው ከግድያው ሙከራ ሕይወታቸውን የጠበቀችው የፋጢማው እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም እንደ ነበረች ተናግረዋል፡፡ ይኸውም እርሷ በመገለጽ የጥይቱ መርዝ እንዲከሽፍ እንዳደረገችውና ወደ ሆስፒታል በሩጫ ሲወሰዱ አእምሮአቸውን ሳይስቱ እርሷን እየተመለከቱ እንዲቆዩ እንደ ረዳቻቸውም ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ተናግረው ነበር፡፡

 

የፋጢማ እመቤታችን እጅግ ቅድስት ማርያም የመጀመሪያው ቤተመቅደስ ሥራ የተጀመረው እ.አ.አ. በ1928 ዓ. ም. ሲሆን የተመረቀው እ.አ.አ. በጥቅምት 7 ቀን 1953 ዓ. ም. ነበር፡፡ የፋጢማ እመቤታን አጅግ ቅድስት ማርያም አክብሮት እንዲስፋፋ አያሌ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ከፍተኛ አስትዋጽኦ እንዳደረጉ የሚታወስ ነው፡፡ ለምሳሌ ርእሰ ሊቀነ ጳጳሳት ፒዮስ 12ኛው (1939-1958) እ.አ.አ. በግንቦት 13 ቀን 1942 ዓ. ም. እና በህዳር 1 ቀን 1950 ዓ.ም. እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም አክብሮት እንዲስፋፋ በሐዋርያዊ መልእክታቸው አደራ ብለዋል፡፡ እንዲሁም ደግሞ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ብፁዕ ጳውሎስ 6ኛው (1963-1978) በግንባት 13 ቀን 1967 ዓ. ም. ከእህት ሉቺያ ጋር አብረው ለመጸለይ ወደ ፋጢማ መሄዳቸው ይታወሳል፡፡ በበኩላቸው ደግሞ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ (1978-2005) እ.አ.አ. በግንቦት 13 ቀን 1981 ዓ. ም. ከተደረገባቸው የግድያ ሙከራ ሕይወታቸውን ስለ ጠበቀች የፋጢማ እመቤታችን እጅግ ቅዱስት ድንግል ማርያምን ለማመስገን እ.አ.አ. በግንቦት 12 ቀን 1987 ዓ. ም. እንደ መንፈሳዊ ተጓዥ ወደ ፋጢማ በመሄድ በማግሥቱ የዓመታዊ ክብረ በዓሏ ተካፋይ እንደነበሩ ይነገራል፡፡ በዚያም አጋጣሚ ማለትም እ.አ.አ. በግንቦት 13 ቀን 1987 ዓ. ም. የሰውን ልጅ በሙሉ አደራ ለእመቤታችን እጅግ ንጹሕ ልብ እንደ ሰጡም ይነገራል፡፡ የፋጢማ ቤተመቅደስ ዋና ዓመታዊ ክብረ በዓል የሚከበረው እ.አ.አ. በግንቦት 13 ቀንና በጥቅምት 13 ቀን ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ዓመቱን በሙሉ በበጋ ወራት ብዙ ምእመናን ወደ ፋጢማ መንፈሳዊ ጉዞ እንደሚያደርጉ ይታወሳል፡፡ በተለይም ደግሞ እ.አ.አ. በየዓመቱ በግንቦት 13 ቀን እና በጥቅምት 13 ቀን 75000 ያህል መንፈሳውያን ተጓዦች በትንሿ የፋጢማ ከተማ እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያምን ለማክበር ይሰበሰባሉ፡፡ ሕይወታችን ለፋጢማዋ እጅግ ንጹሕ የእምቤታችን ቅዱስ ልብ የተለየ ይሁን፡፡ የፋጢማዋ እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ሕይወታችንን ከክፉ አደጋ ሁሉ ትታደግልን፡፡

አባ አንጦንዮስ አልበርቶ (ካፑቺን)

   
© Ethiopian Catholic Secetariat